ዐቢይ አህመድ አይተኬ መሪ ናቸውን
መግቢያ ፦
ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን የታየው የፖለቲካ ሂደት ከመቼውም ጊዜ በላይ መርህየለሽ የሆነ የጎራ መደበላለቅ የታየበት ነበር። በተለይም “ዐቢይ አሻጋሪያችን ነው” በማለት በዶ/ር ዐቢይ ዙሪያ ተሰባስቦ የጦርነቱ ዋና ደጋፊና ተዋናይ ሆኖ የታየው የፖለቲካ ጎራ የጋራ ጠላት እንጂ ከህዝብ ጥቅም ጋር የተያያዘ የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ስላልነበረው የሀገሪቱን የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ቅጥ-አልባ አድርጎት ቆይቷል።
ቀደም ሲል ከእነ አቦይ ስብሃት ከእስር መፈታት ጋር ተያይዞ፣ ከዚያም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሲፈረምና የሰሜኑ ጦርነት ሲቆም ይህንን መርህ-የለሽ ጎራ አስተሳስሮት የነበረው “የጋራ ጠላት” አጀንዳ ከመኖር ወደ አለመኖር ተቀይሯል። በዚህም ምክንያት የአምስት ዓመቱ የጎራ መደበላለቅ ወደ እውነተኛ ፈርጁ ማለትም ወደ ቅድመ 2010 ዓ.ም ተመልሶ ሲሸጋሸግ እያየን ነው። ከጦርነቱ መቆም በኋላ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ እየመጣ እንደሆነ ምልክቶች ሲታዩ የነበረ ቢሆንም የመጣው ለውጥ ራሱን በጎላ ሁኔታ የመግለፅ ዕድል ያገኘው ግን ከወቅቱ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ችግር ጋር ተያይዞ ነው ማለት ይቻላል። ማለትም መንግስት በቤተክርስቲያኗ ላይ ያሳየው አይን ያወጣ ጣልቃ-ገብነት ቀድሞውንም ጎራቸውን ለመለየት ዳርዳርታ ላይ ለነበሩ የፖለቲካ ኃይሎችና ግለሰቦች ወደ እውነተኛው ጎራቸው ለመሸጋገር ጥሩ ሰበብና ዕድል የፈጠረላቸው አጋጣሚ ሆኗል። “ጊዜ እንስጠው”፣ “ሌሎች አላሰራ ብለውት ነው”፣ “የባሰ አደጋ እንዳይመጣብን ብለን ነው” ወዘተ… በሚሉ አመክንዮ-አልባ ሰበቦች ዶ/ር. ዐቢይን በጭፍን ሲደግፉ የነበሩ ሁሉ ዛሬ ላይ ቀንደኛ የዶ/ር ዐቢይ ተቃዋሚ በመሆን የሸሚዛቸውን እጄታ ሲሰበስቡ እያየን ነው። ይህ ለውጥ በሰሞኑ የአድዋ በዓል አከባበር ምክንያትም የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
እንደ ፖለቲካ ጎራም በጦርነቱ ወቅት የዶ/ር ዐቢይ ዋና ደጋፊ የነበሩ የኢትዮጵያ እና የአማራ ብሔርተኞች በሚገርም ፍጥነት የዶ/ር ዐቢይ ቀንደኛ ተቃዋሚ ሲሆኑ፤ በተቃራኒው ደግሞ በጦርነቱ ወቅት የዶ/ር ዐቢይ ዋና ተቃዋሚና ተፋላሚ የነበሩት የንዑስ ብሔር ብሔርተኞች ለማመን በማይቻል ሁኔታ በቤተክሪስቲያኗ ላይ የተቃጣውን ጥቃት እንደተገቢ ድርጊት በመቁጠር የመንግስት ደጋፊ ለመሆን ሲሞክሩ ታይቷል። የአማራ ብልጽግና የሰሞኑ የፈራ-ተባ ዳርዳርታም ይህንኑ እውነታ የሚያሳይ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ግን ዶ/ር ዐቢይ የተለየ አዲስ አቋም ይዘው ወይም አዲስ ጥፋት በመስራታቸው አይደለም። ይልቁንም ጭፍን ደጋፊዎቻቸው ዶ/ር ዐቢይን የሚያዩበትና የሚመዝኑበት ዐይን እየተቀየረ በመምጣቱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፊት ሌላ አሳሳች ካርድ ሲመዙ (በእኔ እምነት አንድ ሁለት ካርድ የቀራቸው ይመስለኛል) እንደገና አቋማቸው ሊቀለበስ የሚችልና ግራ-አጋቢ የሆነ አቋም ይዘው የቀጠሉ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችና ግለሰቦችም አሁንም አሉ። እነዚህ ኃይሎች ወደ እውነታው እንዲመጡ አስፈላጊውን ግፊት ማድረግ፣ ዘግይተውም ቢሆን ወደ እውነታው የመጡትን ወገኖች ደግሞ “እስከ አሁን የት ነበራችሁ?” በማለት ማሸማቀቅ ሳያስፈልግ በጸጋ መቀበል አስፈላጊ ይሆናል። ስለ ስህተታቸው ህዝብን ይቅርታ ቢጠይቁ ክብርና ጥቅሙ ለራሳቸው ስለሆነ የግድ እነርሱን ንስሃ ካልገባችሁ ብሎ ለመጫን መሞከሩ ብዙም ፋይዳ የለውም።
የሁለቱም የፖለቲካ ጎራዎች ወዳጅና ወኪል በመምሰል የማይቻለውን ለመሆን አጉል ሲዋትቱ የከረሙት ዶ/ር ዐቢይ አህመድም አሁን ላይ ዋና የድጋፋቸው መሰረት ከነበረው ከኢትዮጵያና ከአማራ ብሔርተኛ ኃይሎች ራሳቸውን በመነጠል የንዑስ ብሔር ብሔርተኛው ወኪል ወደመሆን አቅጣጫ አዘንብለዋል። ይህ ዝንባሌአቸው እሰከመቼ በቦታው ላይ ሊቆይ እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ከዚህ በኋላ ግን በዚህ አጉል የብልጣብልጥ መንገድ ያልተገባ የህዝብ ድጋፍ የማግኘት ዕድላቸው እየጠበበ መጥቷል። በተጨማሪም ከራሳቸው የስልጣን የበላይነት ባለፈ የየትኛውም ህዝብ ጥቅም አስከባሪና መርህ-ያላቸው ሰው እንዳልሆኑ የበለጠ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በአጭሩ አንዳንዶቻችን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እውነተኛ ማንነት ለህዝብ ለማሳወቅ ለአራት ዓመታት ያህል ደክመን ያልተሳካልንን ጥረት የፕሪቶሪያው ስምምነትና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጠረው ችግር በአቋራጭና በማይታመን ፍጥነት አሳክቶታል።
ደጋግሜ እንደምለው ‘የወቅቱ የፖለቲካ ትግል መልካም ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ በቅድሚያ ህዝቡ በዶ/ር ዐቢይ የአመራር ሚና ከልቡ ተስፋ መቁረጥ አለበት’። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያሳየው ያለው መረዳት ለወደፊቱ ትግል ውጤታማነት ጠቃሚ ግብዓትና መደላድል ሆኖ የሚያገለግልና እንደ ትልቅ የትግል ውጤት ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሰሞኑ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ችግር በራሱ እጅግ አሳዛኝና ፈፅሞ ሊከሰት የማይገባው ቢሆንም ከቤተክርስቲያኗ የወደፊት ህልውናም ሆነ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ አኳያ ግን ብዙ ትምህርት ያስተማረን ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
ከእነዚህ መካከልም፡-
✓ የፖለቲካና የሃይማኖት ጉዳይ ሲደበላለቅ በአንድ ሀገር ላይ ምን ያህል ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል፣
✓ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ሰዎችን ምን ያህል የማነሳሳትና የማስተባበር አቅም እንዳለው፣ አንድ ህዝብ ለመብቱ መከበር ቀናዒ ከሆነና ከተባበረ የጦር መሳሪያ ማንሳት ሳያስፈልገው ምን ያህል በሰላማዊ መንገድ መብቱንና ጥቅሙን ማስከበር እንደሚችል፣
✓ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ሁሉ የመከፋፈል የፖለቲካ ሂደት በኋላ ዛሬም የብሔር ማንነትን የተሻገረ ጠንካራ የጋራ ማንነትና አንድነት ያለን ስለመሆኑ፣
✓ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመሪዎቿና በተከታዮቿ ጥንካሬ ለጊዜው ከተቃጣባት የህልውና ጥቃት ራሷን መታደግ ብትችልም ወደፊት ለከባድና ለረቀቀ ጥቃት የበለጠ ተጋላጭ ሆና እንደምትቀጥል፣
✓ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጊዜው ስልታቸውን ለመቀየርና ወደኋላ ለማፈግፈግ ቢገደዱም ዛሬም ሆነ ወደፊት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባታቸውን እንደማያቆሙ፣
✓ ሀገሪቱን እየመራ ያለው መንግስት በቀላሉና በሆነ ድንገተኛ ቀውስ በማንኛውም ጊዜ ሊፈራርስ የሚችልና እንዲህ አይነቱ አደጋ ሲከሰት ግን ሀገረ-መንግስቱን ከህልውና አደጋ ለመታደግ የሚያስችል የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል እንደሌለ በግልጽ አስተምሮናል። ሂደቱ እግረመንገዱንም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ታሪካዊነትና ማንነት ለትውልዱ በማሳወቅ ረገድ ጥሩ እና ከፍተኛ ዕድል ፈጥሮ አልፏል።
ይሁንና፣ በዶ/ር ዐቢይ ተስፋ ያልቆረጡ አንዳንድ ደጋፊዎቻቸው በተደጋጋሚ የሚያነሱት አንድ ጥያቄ አንዳንድ የእርሳቸውን ተቃዋሚዎችና የውጭ መንግስታትን ጭምር ሲያደናግር ወይም ሲያስጨንቅ አያለሁ። ይኸውም “ዶ/ር ዐቢይ ከስልጣን ቢወርዱ ማን ይተካቸዋል?” የሚለው ጥያቄ ነው። በሌላ አባባል ዶ/ር ዐቢይ ከስልጣን ቢነሱ ሀገሪቱ ወደ ባሰ ቀውስ የመግባት ወይም የመፍረስ አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የሚያሳይ ነው። በእኔ አመለካከት በዚህ ጥያቄና ስጋት ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ካልተፈጠረ በስተቀር ህዝቡ የቱንም ያህል የዶ/ር ዐቢይን እውነተኛ ማንነት ቢረዳም ትግሉ በቀላሉና በሚፈለገው ፍጥነት ለውጤት ሊበቃ አይችልም። ስለሆነም የዚህ የዛሬ መጣጥፌ ዋና ዓላማ ለዚህ ጥያቄና ስጋት የራሴን መልስና አስተያየት ለመስጠት መሞከር ይሆናል።
1.ዶ/ር ዐቢይ ብቁ መሪ ናቸውን?
“ዶ/ር ዐቢይ ከስልጣን ቢወርዱ ማን ይተካቸዋል?” የሚለውን ጥያቄ በብቃት ለመመለስ በቅድሚያ የዶ/ር ዐቢይን የመሪነት ብቃት በጥቅሉና በአጭሩ መገምገም ያስፈልጋል። ዶ/ር ዐቢይ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት እንደማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገርን እንዲመሩ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የነበረችውን ሀገር በአግባቡ አረጋግተው መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት ታሪካዊ ሀላፊነት እንዲወጡ ነበር። ሆኖም እንኳንስ ሀገሪቱን አረጋግተው መዋቅራዊ ሽግግር ሊያመጡ ይቅርና “ተክቼዋለሁ” ከሚሉት የ27 ዓመቱ ስርዓት በባሰ ሁኔታ ሀገሪቱን ከድጡ ወደ ማጡ ሊባል ወደሚችል አዘቅጥ ውስጥ ከትተዋታል።
ዶ/ር ዐቢይን “ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች” በማለት በየመድረኩ በሚያሰሙት ባዶ ንግግር ሳይሆን በተጨባጭ ተግባራቸው ልንገመግማቸው ስንሞክር እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሀገሪቱ ከየት ወዴት እንደተሸጋገረች ለመረዳት ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም። ይህንንም ከቀጣዮቹ አራት መሰረታዊ መመዘኛዎች አንጻር ልንመልከተው እንችላለን…
1.1. ከኢኮኖሚ አኳያ ፦
የሀገር ውስጥ አጠቃላይ የምርት እድገት ከ50% በላይ ሲያሽቆለቁል፣ የዋጋ ግሽበት በአማካይ በ300% ሲያሻቅብ፣ የውጭ ምንዛሬ ምጣኔ ከ100% በላይ ሲንኮታኮት፣ የስራ አጥነት ቁጥር ከ50% በላይ ሲመነደግ፣ መዋቅራዊ ሙስና በከፍተኛ መጠን ሲንሰራፋ፣ ከሁሉም በላይ የሚላስ የሚቀመስ የሌለውና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ህዝብ ቁጥር ከ20 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ታይቷል።
1.2. ከፖለቲካ መብትና ከፍትህ አኳያ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች ያለ በቂ መረጃ በግፍ ሲታሰሩ፣ የፓርቲዎች ህጋዊ እውቅና በህገ-ወጥ መንገድ ሲሰረዝ፣ የቀላል ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ወንጀሎች ተጠያቂነት ሲጠፋ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ሃሣብን ወይም ተቃውሞን መግለጽ ያለበቂ ምክንያት ሲታገድና ምላሹ ጥይት ሲሆን፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በተደጋጋሚ በራሱ በመንግስት ሲጣሱ፣ የመንግስት መገናኛ ብዙኀን የስም ማጥፊያና የዘር ማጥፋት ወንጀል የመቀስቀሻ መሳሪያ ሲሆኑ፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ ቅጥ ባጣ መጠን ሲደበላለቅ፣ ዳኞች በሀገሪቱ መሪ በአደባባይ “ሌባ” ተብለው ሲሰደቡ፣ በጥቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስርዓተ መንግስቱን ከውሳኔ ሰጭነት ሚና አውጥተው ራሳቸውን ከፓርቲና ከመንግስት ስልጣን በላይ አስቀምጠው የሁሉም ነገር ወሳኝና ፈላጭ ቆራጭ መሪ ሲሆኑ አይተናል።
1.3. ከፀጥታና ከሉዓላዊነት አኳያ
የዜጎች ከቦታ ቦታ በሰላም የመንቀሳቀስ መብት ሲገታ፣ አማራው ህዝብ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ በተደጋጋሚ ሲከለከል፣ የትግራይ ህዝብ በራሱ መንግስት ለሁለት ዓመት ተከቦ ለዕልቂት ሲዳረግ፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በጠራራ ፀሀይ ሲገደሉ፣ በኦሮሚያ አባገዳዎች በአደባባይ ሲረሸኑ፣ ዜጎች በሃይማኖትና በብሔር ማነነታቸው በጅምላ ሲገደሉ፣ መስጊዶችና አብያተ ቤተክርስቲያናት በግፍ ሲቃጠሉ፣ በጦርነትና በፖለቲካ ግጭት ምክንያት ብዙ ሚሊዮኖች ሲፈናቀሉና ሲሰደዱ፤ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ሴቶች ሲደፈሩ፣ ገዳዮች በመግደል ብቻ ሳይሆን በአገዳደል የጭካኔ ዓይነት ሲፎካከሩ፣ የራሳችን መንግስት የውጭ መንግስትን ጋብዞ የራሱን ዜጎች በግፍ ሲያስጨፈጭፍ፣ ሉዓላዊነታችንና ግዛታችን በሻዕቢያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን መንግስትና በአልሸባብ ተደፍሮ ዝም ሲባል፣ በታሪካችን አይተነው በማናውቀው መጠን በአንድ የእርስ በርስ ጦርነት ከአንድ ሚሊየን በላይ ህዝብ ሲያልቅና በትሪሊየን ብር የሚገመት የሀገርና የህዝብ ሃብት ሲወድም፣ ከሁሉም በላይ የአንድ ሀገር ህዝብ የሆነው ኢትዮጵያዊ በውስጥ የአስተዳደር ወሰን ጎራ ለይቶ ሲዋጋና እስከ ዘር ማጥፋት የደረሱ ከፍተኛ ዓለም-አቀፍ ወንጀሎች በሀገሪቱ ሲፈጸሙ አይተናል።
1.4. ከዲፕሎማሲ አኳያ
ኢትዮጵያ በአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነትና በዘር ማጥፋት ወንጀል እየተከሰሰች ገጽታዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠለሸበት፣ በፀጥታ ስጋትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሀገሪቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ13 ጊዜ በላይ የተባበሩት መንግስታት የመወያያ አጀንዳ የሆነችበት፣ በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንግድ ግንኙነት፣ እርዳታና ብድር ማዕቀብ የተጋለጠችበት ሁኔታ ሲፈጠር አይተናል።
ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት የነበሩብንን ቀደምት ችግሮች አስወግደው ወደ አዲስና በጎ አቅጣጫ እንዲያሸጋግሩን ታስቦ ቢሆንም እንኳንስ የቀደመውን ችግራችንን ሊያቃልሉልን ከፍ ሲል እንዳየነው በታሪካችን አይተናቸው የማናውቅ በርካታ አዳዲስ ችግሮችን ቀፍቅፈውልናል። ከሁሉም በላይ የስርዓተ-መንግስቱን ስልጣንና ሃላፊነት ሁሉ ቀምተው በብቸኝነት በመያዝ የሀገረ-መንግስቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥለውታል። ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት እንዲኖረን የምንፈልገው የሀገር መሪ ያለፉትን ችግሮቻችንን አቃልሎ ወደተሻለ ሀገራዊ ሁኔታ እንዲያሸጋግረን ከሆነ - ‘በምን መመዘኛ ነው ለዚህ ሁሉ ውድቀትና መከራ የዳረጉንን ዶ/ር ዐቢይን እንደ አንድ ጥሩና ምትክ-የለሽ መሪ ቆጥረን በስልጣን ላይ እንዲቀጥሉ የምንፈልገው?’
በእኔ አመለካከት ዶ/ር ዐቢይ የእሳቸው የስራ ድርሻና ኃላፊነት ያልሆኑና የሀገሪቱን የፋይናንስ ህግ ያልተከተሉ የተወሰኑ በጎ ስራዎችን ያከናወኑ መሆኑን አውቃለሁ። ሆኖም የአንድ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊመዘንባቸው በሚገቡ ስራዎች ስመዝናቸው ግን ለኃላፊነታቸው የሚመጥን የተጨበጠ ስራ አልሰሩም። በደጋፊዎቻቸው ዘንድ እንደከፍተኛ ስኬት የሚነገሩላቸው ስራዎችም የእሳቸው የስራ ድርሻ ካለመሆናቸውና የፋይናንስ ህግን ያልተከተሉ ከመሆናቸውም በላይ የሀገሪቱን የችግሮች ቅደም ተከተል የረሱ በመሆናቸው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድክመት መገለጫዎች እንጅ እንደ በጎ ውጤቶች ልናያቸው የሚገቡ አይደሉም።
ስለሆነም ዶ/ር ዐቢይ ምንም ዓይነት የመሪነት ተሞክሮና ታሪክ ሳይኖራቸው ከጅምሩ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸው፣ ከተመረጡም በኋላ ምን ያህል ደካማ እና አውዳሚ መሪ መሆናቸው በተግባር እየታየ ለአምስት ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ እንዲቆዩ መደረጋቸው፣ ይህም አልበቃ ብሎ ወደፊት ሀገሪቱን የመምራት ዕድል የሚሰጣቸው ከሆነ ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ሀገር እንዲፈርስ የመወሰንን ያክል እጅግ ከፍተኛ ታሪካዊ ስህተት ይሆናል። ተዘርዝሮ የማያልቅ ድክመት ያለባቸውና ከሁሉም በላይ በስልጣን ዘመናቸው በአንድ የእርስ በርስ ጦርነት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዲያልቅ ያደረጉ መሪ ሆነው እያለ ዶ/ር ዐቢይን ዛሬም ላይ እንደ አንድ ጥሩና ብቁ መሪ ቆጥረው የሚደግፏቸው ዜጎች መኖራቸው የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን አጥንት ድረስ ሠርፆ የሚያም ነው።
ከዚህ ቀደም በአንድ ቃለ-መጠየቅ ላይ እንደገለጽኳቸው በእኔ ምልከታ እንደ ዶ/ር ዐቢይ ፡-
✓ ህግን እየጣሰ → እንደ ህግ አክባሪ
✓ መብትን እያፈነ→እንደ ዲሞክራት
✓ ኢኮኖሚን እያወደመ → እንደ አበልጻጊ
✓ ተረት እያወራ →እንደ አዋቂና ሊቅ
✓ ውሸት እየተናገረ →እንደ ሀቀኛ
✓ ጦረኝነትን እያራመደ→ እንደ ሰላም ወዳድ
✓ የትግል ጓዶቹን እየካደ →እንደ ታማኝ
✓ሀገሩን በውጭ ወራሪ እያስደፈረ →እንደ ሀገር ወዳድና ጀግና
✓ ከፋፍሎ የመግዛትን ስልት እያራመደ → እንደ አንድነት ጠበቃ
✓ጥላቻን እየሰበከ →እንደ ሃይማኖታዊ ሰው
✓ ህዝብን እየጨፈጨፈ →እንደ ሩህሩህና የህዝብ ልጅ
✓ ሀገሪቱን አኬል-ዳማ እያደረገ → ፈጣሪ እንደላከው መሲህ የተወደደና የተመለከ መሪ በአለም ላይ እንደ ዶ/ር ዐቢይ ታይቶ አይታወቅም። ይህ ለምን እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት ለመስጠት እንደ እኔ ፖለቲከኛ መሆን ሳይሆን የስነ-ልቦና አዋቂ መሆንን ወይም ጠንቋይና ነቢይ ነኝ የማለትን ድፍረት ይጠይቃል።
በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ዶ/ር ዐቢይ በየአደባባዩ ስለ ሀገሪቱ ታላቅነትና ብልጽግና በሚያወሩት ባዶ ቃል ሳይሆን የአምስት ዓመት ዕድሜ ተሰጥቷቸው በተግባር በሰሩት ስራ ሲመዘኑ እንኳንስ ብቁ መሪ ሊባሉ ይቅርና እንዲያውም ‘የሀገሪቱ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት’ ተደርገው መታየት ያለባቸው መሪ ናቸው።
2. ዶ/ር ዐቢይ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሚሆኑት እንዴት ነው?
በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፍኩት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ዶ/ር ዐቢይን “የብሔራዊ ደህንነት ስጋት” አድርጌ መግለፄ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ጥያቄና ብዥታ ሲፈጥር አይቻለሁ። እርግጥ ነው ብዙውን ጊዜ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ተደርገው በተለምዶ የሚታዩት ሌሎች ውጫዊና ውስጣዊ ጉዳዮች በመሆናቸው በዚህ ረገድ ጥያቄ ወይም ብዥታ መፈጠሩ የማይጠበቅ አይደለም። የሚገርመው ዶ/ር ዐቢይ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት መባላቸውን የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች ፓትሪያሪኩን የብሔራዊ ደህንነት ስጋት አድርገው የሚያዩ ሰዎች መሆናቸው ነው።
አንድ ብቃት የሌለው ደካማ ወይም አምባገነን መሪ በሆነ የታሪክ አጋጣሚ በአንድ ሀገር የመሪነት ስልጣን የመያዝ ዕድል ሲያገኝ ለሚመራው ሀገር የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የመሆን ዕድል አለው። አንድ የሀገር መሪ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅምና ደህንነት በላይ ለራሱ የፖለቲካ ስልጣን የበለጠ ቀናዒ ከሆነ፣ በዚህም ምክንያት የ“ከፋፍለህ ግዛው” ስልት በመጠቀም ህዝቡን እርስ በእርስ የሚያጋጭና የሚያዋጋ ከሆነ፣ የሚመራዉን ሀገር ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ወረራ የመከላከል አቅም ከሌለው፣ በሚመራው ሀገር ውስጥም ሰላምን እና የህግ የበላይነትን ማስፈን ካልቻለ፣ በተለይም ጠብ-አጫሪና ጀብደኛ መሪ ከሆነ በሀገሩ ላይ አደጋ የማስከተል ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዙሪያ የተከሰተውን ችግር በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚንስትሮች ካቢኔ አደረጉት የተባለውን ንግግር እንደ አንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ብናይ ያልተጠና ንግግር የሚያደርግ ስሜታዊ መሪ ምን ያህል አንድን ሀገር በድንገት ወደ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ያሳየናል።
ስለሆነም ዶ/ር ዐቢይን የመሰለ፡-
✓ ለአምስት ዓመት በስልጣን ላይ ተቀምጦ የህግ የበላይነትን ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስከበር ያልቻለ፣
✓ “ድሃ ሀገር ሉዓላዊነት የለውም” በማለት የተሳሳተ አመለካከት የሚያራምድ፣
✓ “ከጥቃት አድነን” ብለው ለሚጠይቁት ዜጎች “እኔ የሰፈራችሁ ሚሊሻ አይደለሁም” በማለት የሚሳለቅ፣
✓ ሀገሪቱ በጦርነት እየተናጠች ባለችበት ወቅት ጊዜውንና ትኩረቱን በመናፈሻና በቤተ መንግስት ግንባታ የሚያጠፋ፣
✓ በብዙ መቶ ሺዎች እያለቁበት ያለን ጦርነት “መለማመጃችን ነው” በማለት የሚቀልድ፣
✓ ከ20 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በተራበበትና የቦረና ህዝብ እያለቀ ባለበት ሀገር ስንዴ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ አለብኝ ብሎ የሚቃዥ፣
✓ “መቶ ሺዎች ያልቃሉ እንጂ ስልጣኔን አልለቅም፣ የእኛ ግድያ ከኢህአፓ ዘመን ግድያ በበዙ እጥፍ የበለጠ ይሆናል” በማለት በአደባባይ የሚዝትና የሚያስፈራራ፣
✓ የሚመራውን ህዝብ “ጠላት” እና “ደጀን” ብሎ የሚፈርጅና የሚከፋፍል፣
✓ “አዲስ አበባ ከፍተኛ ኦሮሞ-ጠል የሆነ ህዝብ አለ”፣ “ኦርቶዶክስና እስልምና ለብልጽግና እንቅፋት ናቸው” በማለት ሃይማኖታዊና ብሔር-ተኮር ቅስቀሳዎችን ሆን ብሎ የሚያካሂድ፣
✓ “ገና ብዙ መስጂድና ቤተክርስቲያን ይፈርሳል፣ ብዙዎችም ገና ወደ ፊት ይሞታሉ” በማለት ውድመትንና እልቂትን ለህዝብ የሚያለማምድ፣
✓ “ግብጽ ሄጄ አጥፍቶ ጠፊ ለመሆን”፣ “ለአሜሪካ ተዋግቼ ለመሞት” ፍላጎት አለኝ ብሎ በስሜታዊነት የሚናገር፣ ራሱን እንደ ፖለቲካ መሪ ብቻ ሳይሆን ልዩ መለኮታዊ ተልዕኮ አንዳለው ንጉስ የሚቆጥር፣
✓ የውጭ ወራሪ ጋብዞ የራሱን ህዝብ የሚያስጨፈጭፍና ሀገሩን በውጭ ኃይል አስወርሮ ዝምታን የሚመርጥ፣
✓ “የመንግስት ባለስልጣን እያለሁ ከአማፂ ኃይሎች ጋር በድብቅ እገናኝና እተባበር ነበር” ብሎ የሀገር ክህደት ወንጀል መፈፀሙን በድፍረት የሚናገር፣
✓ “ንግግሬ ሁሉ ፊርማ ነው” በማለት ራሱን ከፓርቲና ከመንግስት ስልጣን በላይ አድርጎ የሚያይ፣
✓ በአጠቃላይ ግጭትና ቀውስን ሆን ብሎ እራሱ እየፈጠረ፣ በፈጠረው ግጭትና ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ እልቂት ከደረሰ በኋላም እንደገና ራሱን እንደ አስታራቂ፣ አዳኝና መፍትሄ ሰጪ አድርጎ ለማቅረብ የሚሞክር የመሪነት ትርጉም ያልገባው “መሪ” የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ቀዳሚና ዋና ስጋት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው ።
እንዲያውም ዶ/ር ዐቢይ የወደፊት የሀገሪቱ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ብቻ ሳይሆኑ በእስካሁኑ የስልጣን ዘመናቸው ግጭትና ጦርነትን እንደ ዋና የስልጣን ማስጠበቂያ ስልት በመጠቀም በሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ለትውልድ የሚሸጋገር ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ መሪ ናቸው። ወደፊትም ተገማች ባልሆነው፣ ስሜታዊነት በሚያጠቃው፣ ግላዊና እወደድ ባይ በሆነው የአመራር ስልታቸው በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ሊፈጽሙ የሚችሉ አደገኛ መሪ ናቸው። ስለሆነም የእሳቸው ስልጣን ላይ የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ አብዝቶ የሚያሳስበን ደካማና አምባገነን መሪ ስለሆኑ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ተጠምዶ እንደተቀመጠ ተቀጣጣይ ፈንጂ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ተጨባጭ፣ ቀዳሚና ዋና ስጋት ስለሆኑ ነው።
3. ዶ/ር ዐቢይ አይተኬ መሪ ናቸውን…?
በመግቢያዬ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት “ዶ/ር ዐቢይ ከስልጣን ቢወርዱ ማን ይተካቸዋል?” የሚለው ኢ-ምክንያታዊ ጥያቄ በአግባቡ ካልተመለሰ በስተቀር ወደፊትም የለውጥ እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። በእኔ በኩል ብዙውን ጊዜ እንዲህ አይነቱ ጥያቄ የሚያጋጥመኝ “በእርሳቸው ተስፋ መቁረጥ አለብን” ወይም “የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት” የሚል የመፍትሔ ሃሣብ ሳቀርብ ስለሆነ ርዕሰ ጉዳዩን ከእነዚህ የመፍትሄ ሃሣቦች ጋር አያይዤ ለማየት እሞክራለሁ።
ከአሁን በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፍኩት ግልጽ ደበዳቤ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሀገሪቱ ከገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ ወጥታ ወደ በጎ አቅጣጫ እንድትሸጋገር ከተፈለገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእጃቸው ያለው አማራጭ ሁለት ነው።
የመጀመሪያው የዶ/ር ዐቢይ አማራጭ - ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሀገሪቱ ከመፍረሷ በፊት ሃቀኛና ሁሉን አቀፍ የሆነ ሀገራዊ የውይይትና የድርድር ሂደት /National Dialogue/ በአስቸኳይ መጀመርና ሀገሪቱ ወደ እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት መሸጋገር የምትችልበትን አቅጣጫ ማስያዝ ነው። በዚህ የሽግገር ሂደት ሊከናወኑ የሚገባቸው የለውጥ ሂደቶች ምን ምን ናቸው? የሽግግር ሂደቱስ በማንና እንዴት ሊመራ ይችላል? የሂደቱ የመጨረሻ ውጤትስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ የሚችሉትም በዚህ ሀገራዊ የውይይትና የድርድር ሂደት ይሆናል።
በሌሎች ሀገሮች ከታዩ ልምዶች እንደምንገነዘበው የውይይትና ድርድር ሂደቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅን መፍጠር፣ የሽግግር ጊዜ ፍትህን ማስፈን፣ የህግና የተቋማት ማሻሻያን ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ተግባራት እንደሚሆኑ አስቀድሞ መናገር ይቻላል። የውይይትና የድርድር ሂደቱም በአንድ ገለልተኛ የሆነ ልዩ ኮሚሽን ወይም በአዲስ የሽግግር መንግስት እንዲመራ ማድረግ ይቻላል። በእኔ በኩል ለወቅቱ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ የተሻለ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው አዲስ የሸግግር መንግስት ማቋቋም ነው የሚል ጠንካራ አመለካከት አሁንም ያለኝ ቢሆንም እንዲህ አይነቱ ውሳኔ መወሰን የሚገባው ግን በራሱ በሀገራዊ የውይይትና የድርድር ሂደቱ ነው። እዚህ ላይ በእኔ በኩል በጽሁፍ የማቀርባቸው የመፍትሄ ሃሣቦች አማራጭ የውይይት መነሻ ሃሣብ እንዲሆኑ እንጂ እንደ ብቸኛና የመጨረሻ መፍትሄ ተደርገው ተቀባይነት እንዲያገኙ ታስበው የሚቀርቡ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
የለውጥ ሂደቱ የሚካሄደው በልዩ ኮሚሽንም ይሁን በአዲስ የሽግግር መንግስት አማካኝነት፣ ‘የዶ/ር ዐቢይ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይገባል?’ የሚለው ጥያቄም በዚሁ የውይይትና ድርድር ሂደት የሚወሰን ይሆናል። ዶ/ር ዐቢይ እውነተኛ ለውጥ በሀገሪቱ እንዲመጣ ከወሰኑም ሂደቱ የሚያስከትለው ውጤት የእርሳቸውን ስልጣን የሚያሳጣ ከሆነም ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል አስቀድመው መወሰንና መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ማንኛውም የራሱን የስልጣን ጥያቄ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም በላይ አድርጎ የሚያይ መሪ መሰረታዊ ለውጥ በሀገሪቱ ሊያመጣ ስለማይችል ዶ/ር ዐቢይም እንዲህ አይነቱን አቋም ከልባቸው ሳይቀበሉ እውነተኛ ለውጥ በሀገሪቱ ሊያመጡ አይችሉም።
ሁለተኛው የዶ/ር ዐቢይ አማራጭ፡- ሀቀኛና ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት ማካሄድን የማይቀበሉ ከሆነ ለእርሳቸው ስልጣናቸውን እንዳስረከቡት እንደ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ “ሀገሪቱን ማስተዳደር አልቻልኩምና በቃኝ!” ብለው ከስልጣናቸው መልቀቅ ነው። እርሳቸው እንዲህ አይነቱን ደፋርና ጠቃሚ እርምጃ በኃላፊነት ስሜት ለመውሰድ ከበቁም በእሳቸው ምትክ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመረጥና ተገቢውን ለውጥ እንዲያመጣ የማድረጉ ሃላፊነት ቀድሞውንም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የመረጣቸው የብልጽግና ፓርቲ ይሆናል። ዶ/ር ዐቢይ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት በምልዐተ-ህዝቡ ቀጥተኛ ምርጫ ስላልሆነ ብልጽግና ፓርቲ በእጁ ያለውን ስልጣንና መብት በአግባቡ መገንዘብ ከቻለ እሳቸው ፈለጉም አልፈለጉም በቀላሉ ከስልጣን ሊያነሳቸው ይችላል። ይችላልም ብቻ ሳይሆን ሊያነሳቸውም ይገባል።
ከዚህ የምንገነዘበው ከእነዚህ ሁለት አማራጮች በአንዱ ዶ/ር ዐቢይ ስልጣናቸውን ቢለቁ ሊፈጠር የሚችል የስልጣን ክፍተት የሌለ መሆኑን ነው። ማለትም በሁለቱም አማራጮች አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመረጠው ብልጽግና ፓርቲ ከምድረ-ገፅ ጠፍቶ ወይም መንግስት የሚባለው ተቋም ፈርሶ አይደለም። ዶ/ር ዐቢይ በራሳቸው ወይም በፓርቲያቸው ተገደው ስልጣን ቢለቁ ብልጽግና ፓርቲ ሌላ መሪ በምትካቸው መርጦ ወደ አዲስ የሽግግር ሂደት ሊገባ ይችላል። እርሳቸው ፈቃደኛ ሆነው ሃቀኛ የውይይትና የድርድር ሂደት ቢጀምሩና የሂደቱ ውጤት አዲስ የሽግግር መንግስት ማቋቋምን የሚያስችል ከሆነም አዲሱ የሽግግር መንግስት እሳቸውን በመሪነት ይዞ ሊቀጥል (በእኔ በኩል አሁን ላይ የማልደግፈው ቢሆንም)፣ ወይም በእሳቸው ምትክ አዲስ መሪ መርጦ ስለሚተካ በሁለቱም አማራጮች ለሀገር ህልውና ስጋት የሚፈጥር የስልጣን ክፍተት አይኖርም። ይልቁንም ሀገሪቱ ወደ አዲስ የሽግግር ሂደት እንዳትገባ እንቅፋት የሚሆነውም ሆነ ለህልውና አደጋ የሚያጋልጣት የፓርቲና የመንግስትን ሚና በብቸኝነት ተክተው ዶ/ር ዐቢይ በስልጣን ላይ መቀጠላቸው ነው እንጂ ከስልጣን መውረዳቸው አይደለም። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ቢለቁ ሊተካቸው የሚችል ብቁ ሰው እንደሌለና እሳቸው ከስልጣን ከለቀቁ ሀገሪቱ የባሰ አደጋ እንደሚያጋጥማት ተደርጎ በአንዳንድ ደጋፊዎቻቸው የሚቀርበው ሃሣብ አሳማኝ አመክንዮ የለውም። አመክንዮ የሌለው ከመሆኑም በላይ እንዲህ አይነቱ አስተያየት መቅረቡ በራሱ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ በምን ዓይነት የዘቀጠና ተስፋ አስቆራጭ በሆነ የፖለቲካ ንቃተ-ኅሊና ላይ እንደምንገኝ ጥሩ ማሳያ ነው።
ለመሆኑ - ዶ/ር ዐቢይ የትኛውን ጥሩ ውጤት አምጥተውልን፣ ምንስ ያላመጡብን አበሳና መከራ ኖሮ ነው አሳቸው ከስልጣን ቢወርዱ የባሰ ችግር ይመጣብናል ብለን የምንሰጋው? ኢትዮጵያን በሚያህል ትልቅና ታሪካዊ ሀገር ዶ/ር ዐቢይን ሊተካ የሚችል ሌላ ሰው እንደማይኖር አድርጎ ማሰብስ የኢትዮጵያን ህዝብ አብዝቶ መናቅና ኢትዮጵያን የትውልድ መካን አድርጎ ማየት አይሆንምን?
በርግጥም ኢትዮጵያ ዶ/ር ዐቢይን የሚተካ ሰው የሌላት መካን ሀገር ከሆነች እንደ ሀገር የመፍረስ እንጂ የመቀጠል ዕድል አይኖራትም። እንደ እኔ አመለካከት ከሆነ ግን እንኳንስ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ብልፅግና ፓርቲም ወደ ቀልቡ ተመልሶ እራሱን እንደ ድርጅት ማየት ቢጀምር ከዶ/ር ዐቢይ የተሻለ ሰው በውስጡ ፈልጎ ማግኘት የሚቸገር አይመስለኝም። ሀገሪቱማ ከዶ/ር ዐቢይ የማይሻል ዜጋ የላትም ብዬ ለመናገር መድፈሩን ልተወውና ከእሳቸው የተሻሉ ሚሊዮን ዜጎች እንዳሏት ግን ለአፍታም አልጠራጠርም።
ብልጽግና ፓርቲ ለኢትዮጵያ የሚመጥን እውቀት፣ ልምድና ቅንነት ያለው መሪ ማግኘት ባይችልም እንኳ ቢያንስ ግን በህግ የተሰጠውን የስራ ድርሻውን በአግባቡ አንብቦ የተረዳ፣ ራሱን ከመንግስትና ከፓርቲ ስልጣን በታች አድርጎ የሚያይ፣ የሁሉም ነገር አዋቂ እንዳልሆነ የተገነዘበ፣ የህዝብ እልቂት የሚያስደነግጠውና ተጠያቂነትን የሚፈራ በአንፃራዊነት “ደካማ” የሚባል መሪ ቢሾምልን እንኳን ሀገራችን ቢያንስ ከዶ/ር ዐቢይ የአገዛዝ ዘመን በተሻለ ደህንነቷ የተጠበቀ ይሆናል። ወደ አዲስ የሽግግር ሂደት የመግባት ሰፊ ዕድልም ሊፈጥርልን ይችላል። የሀገሩ ንጉሥ ወይም መሪ ሲሞት “ሰማይና መሬት ይገናኛል” የሚለው ዓይነት ሟርት ሁልጊዜም በታሪካችን አብሮ የኖረ ልማድ ነው። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ለዶ/ር ዐቢይ መጠቀም በማንኛውም መንገድ አሳማኝ አመክንዮ ሊኖረው አይችልም።
ከዚህ ውጭ የዶ/ር ዐቢይ “ምትክ የለሽነት” ሊገለጽ የሚችለው “በአመራር ብቃታቸው” ሳይሆን “ለውጥ አደናቃፊና አደጋ ፈጣሪ” በመሆናቸው ብቻ ነው።
መደምደሚያ ፦
አንኳንስ አንድን እንደ ዶ/ር ዐቢይ በስህተትና በጥፋት የተሞላና ስርዓተ መንግስቱን ንዶ ሀገረመንግስቱን ማፍረስ የቀረው መሪ በአንጻራዊነት ጥሩ የሚባልና ከባድ ጥፋት ያላጠፋ የሀገር መሪንም ቢሆን ስልጣን እንዲለቅ መጠየቅ መብት ነው። ዶ/ር ዐቢይን እንኳንስ “ከስልጣን ይውረዱ” “ለፍርድ ይቅረቡ” ብሎ መጠየቅም ፍታሃዊ ጥያቄ ነው። የመኪና ቀበቶ ሳይታጠቅ የተገኘ ጠቅላይ ሚኒስተር (በቅርቡ በእንግሊዝ ሲሆን እንደታየው) ስልጣኑን እንዲለቅ በሚጠየቅበት ዓለምና ዘመን በስልጣን ዘመኑ ከሚሊዮን በላይ ትውልድ እንዲያልቅ ያደረገንና ሀገረ-መንግስቱን እያፈረሰ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ‘ለምን ስልጣን እንዲለቅ ይጠየቃል?’ ብሎ መከራከር ከጭፍን ደጋፊነት የተለየ አሳማኝ ምክንያት የለውም።
ይህንን የምለውም ያለምክንያት ሳይሆን አንዳንድ የዶ/ር ዐቢይ ወዳጆችና ደጋፊዎች ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን እንዲለቁ የሚቀርብን ጥያቄ ከግል ጥላቻ ወይም ከግል የስልጣን ፍላጎት ጋር በተያያዘ የሚቀርብ ጥያቄ አድርገው ለመተቸት ሲሞክሩ ስለምሰማ ነው። ጉዳዩ የአንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ህዝብንና የሀገር ህልውናን የሚመለከት ባይሆን ኖሮ ማናችንም ከዶ/ር ዐቢይ ጋር።የሚያጣላን ሌላ የግል ጉዳይ የለንም። ዶ/ር ዐቢይ ቢያንስ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የመረጣቸውን ፓርቲና የሚመሩትን መንግስት ህግና ስርዓት አክብረው የሚሰሩ መሪ ቢሆኑ ኖሮ የሁላችንም ትኩረት እንደ ስርዓት ሀገሪቱን በሚመራው ፓርቲና መንግስት ላይ በሆነ ነበር።
ነገር ግን ዶ/ር ዐቢይ ራሳቸውን በፓርቲና በፓርላማ እንደተመረጠ የሪፐብሊክ መሪ ሳይሆን እንደ ፍጹማዊ ንጉስ መይም ወታደራዊ መሪ በመቁጠር የሁሉም ነገር የበላይና ፈላጭ ቆራጭ በማድረጋቸው በአሳማኝ ምክንያት ትኩረታችንን በእሳቸው ላይ እንድናደርግ ተገደናል። የእኛ የተቃዋሚዎቻቸው ብቻ ሳይሆን የደጋፊዎቻቸውም የድጋፍ መሰረት በብቸኝነት የተንጠለጠለው በአስተሳሰብ ወይም በተጨበጠ ተግባር ሳይሆን በዶ/ር ዐቢይ ግላዊ ስብዕና ላይ ሆኖ የምናየው ሀገሪቱ በእሳቸው ብቸኛ ቁጥጥር ስር የወደቀች በመሆኑ ነው። ይህንን እውነታም ከኛ ከተቃዋሚዎቻቸው በላይ በዙሪያቸው ያሉና ዶ/ር ዐቢይ በተናገሩ ቁጥር ማስታዎሻ ከመያዝና ራስን ከመነቅነቅ ያለፈ ሚና የሌላቸው የፓርቲና የመንግስት ሹማምንት የበለጠ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ጥርጥር የለኝም።
በመግቢያዬ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በቀዳሚነት የእነ አቦይ ስብሃት ከእስር መፈታትን፣ በመቀጠልም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት፣ በመጨረሻም የሰሞኑን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ችግር ተከትሎ መርህ-አልባው የዶ/ር ዐቢይ የድጋፍ ጎራ በከፍተኛ መጠን ተንዷል። ለትግሉ መጠናከር ዋና እንቅፋት ሆኖ የቆየውና የብዙ ዜጎቻችንን እይታ እንደ ሞራ ጋርዶት የቆየው ዶ/ር ዐቢይን የማምለክ “አዚም” መገፈፉ አንድ ትልቅ ስኬት ነው። ነገር ግን የወደፊቱ ትግል የሀገሪቱን መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሚያስታርቅ የሃሣብ ጥራትና ጠንካራ ድርጅታዊ አቅም ባለው ሰላማዊ ትግል ካልተመራ በስተቀር ለዘላቂ ውጤት ሊበቃ አይችልም። የወደፊቱ ትግል ለዘላቂ ስኬት እንዲበቃም ምን ዓይነት የትግል ስልት መከተል።አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳትም በሚከተሉት የተለያዩ፣ ነገር ግን ተያያዥነት ባላቸው የትግል የቅደም ተከተል ጠገጎች ዙሪያ ተገቢ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
✓ ጠገግ አንድ
ስለ ወደፊቱ ትግል ስናስብ በአንድ ጉዳይ ላይ የጠራ ግንዛቤ መያዝ አለብን። ይኸውም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በአንድ ግለሰብ ቁጥጥር ስር የወደቀ አገዛዝ እንጂ ስርዓታዊ የሆነ አገዛዝ የሌለ ስለመሆኑ ነው። 27 ዓመት ስንታገለው የኖርነው የአገዛዝ ስርዓት.በዶ/ር ዐቢይ ተጠልፎ ከከሸፈ ሰንብቷል። አሁን እየታገልን የምንገኘው ከአንድ የአገዛዝ ስርዓት ጋር ሳይሆን የስርዓተ-መንግስቱን ስልጣንና ሃላፊነት ቀምተው የራሳቸውን የበላይነት ካረጋገጡት ከዶ/ር ዐቢይና በዙሪያቸው ከሚገኙ “ክሊኮች” ጋር ነው። የነበረው ስርዓተ-መንግስት ባለበት እንዲቀጥል፣ ወይም በውስጡ የያዛቸው አላስፈላጊ ህግጋቶችና ተቋማት እንዲሻሻሉ ወይም እንዲለወጡ የምንፈልግ የግራ ቀኙ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳችን ሌላችንን አሸንፈን ቆመንለታል የምንለውን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችለን የፖለቲካ ዐውድ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የለም። ማለትም አሁን ላይ በማንኛውም ማንነት ወይም ርዕዮተ-ዓለም ተቧድነንና ተከፋፍለን የምናካሄደው ትግል ትርጉም የለሽ ነው። እንዲቀጥል ወይም እንዲለወጥ የምንታገለው ስርዓተ መንግስት ፈራርሶ የቀረው ነገር የሀገረ-መንግስቱ ህልውና ማጣት እንደሆነ በአግባቡ መረዳት ከቻልን ከዶ/ር ዐቢይና ደጋፊያቸው ከሆነው “ክሊክ” ውጭ ያለው የፖለቲካ ኃይል በሙሉ ሀገረ-መንግስቱን ከመፍረስ የማዳኑ ትግል አጀንዳ የጋራ ባለቤት መሆን ይኖርበታል።
አንድ በድንገቴ የታሪክ አጋጣሚ ስልጣን እጁ ላይ የወደቀለት አምባገነን መሪ ለዘመናት የኖረውን ሀገረ-መንግስት ሲያፈርሰው ዝም ብሎ ማየት ሁላችንንም በታሪክና በትውልድ ፊት ተጠያቂ የሚያደርገን ጥፋት ነው። የፖለቲካ ትግላችን ህገ-መንግስቱን ለማጽናትም ይሁን ለማሻሻልና ለመለወጥ፣ ለአንድነትም ይሁን ለመገንጠል፣ ለፌደራሊዝምም ይሁን ለአሀዳዊነት ወዘተ… ሀገረ-መንግስቱ ለይቶለት ከፈረሰ በኋላ የማናችንም አላማና ፍላጎት ሊሳካ የሚችልበት ዕድል ስለሌለ የትግሉ ባለቤት መሆን የሚገባው ምልዐተህዝቡ ነው። ስለሆነም ማንኛውም የወቅቱ የጎንዮሽ ግጭትና ትግል ለጊዜው ቆሞ የሁላችንም የትግል ትኩረት በዶ/ር ዐቢይና ደጋፊያቸው በሆነው ፀረ-ስርዓት “ክሊክ” ላይ መሆን አለበት። በአሁኑ ወቅት በልዩነቶቻችን ላይ እያካሄድን ያለነውን ወቅቱን ያልዋጀ የጎንዮሽ ትግል ሀገረ-መንግስቱን ከመፍረስ ካዳንነው በኋላ እንደገና ልንመለስበት እንችላለን።
የሀገራችን የፖለቲካ ችግር እጅግ ውስብስብ ስለሆነ ዶ/ር ዐቢይ ከስልጣን ስለወረዱ ብቻ በቀላሉ ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ የማይቻል መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን የእሳቸው ከስልጣን መውረድ ሀገሪቱ ወደ አዲስ የለውጥ አቅጣጫ እንድትገባ አንድ ዕድል የሚፈጥርልንና የሀገሪቱን የአደጋ ተጋላጭነትም በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ የሚያስችለን ይሆናል። ስለሆነም የትግላችን የመጀመሪያ ርብርብ ዶ/ር ዐቢይ በእጃቸው ከሚገኙ ሁለት የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ አንዱን እንዲቀበሉ ማድረግ ሊሆን ይገባል። ማለትም የራሳቸውን የስልጣን እጣ-ፈንታ ጭምር ሊወስን የሚችል ሃቀኛና ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የውይይትና ድርድር ሂደት በአስቸኳይ እንዲጠሩ፣ ይህንን ማድረግ ካልቻሉም ሀገሪቱን በአግባቡ መምራት እንዳቃታቸው ተገንዝበው በፍቃዳቸው ስልጣናቸውን እንዲለቁ አስፈላጊውን ግፊትና ጫና ሁሉ ማድረግ መቻል ነው።
✓ ጠገግ ሁለት
ከዚህ በላይ በጠገግ አንድ ላይ የተጠቀሰው የትግል አቅጣጫ በሁለት ምክንያቶች ስኬታማ ያለመሆነ ዕድል ሊኖረው ይችላል። በአንድ በኩል የዕድሜ ልክ ቤተ-መንግስት በመገንባት ላይ የሚገኙትና በብዙ የወንጀል ድርጊቶች እጃቸውን ያስገቡት ዶ/ር ዐቢይ እንኳንስ በጥያቄና በቀላል ግፊት በመቶ ሺዎች የሚያልቁበት የህዝብ ትግል ቢካሄድም ስልጣናቸውን የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌላቸው ራሳቸው ቁርጡን ነግረውናል። በዚህም ምክንያት ከአሁን በኋላ ዶ/ር ዐቢይን የመፍትሄአችን እንቅፋት እንጂ የመፍትሄአችን አካል አድርገን የምናይበት ዕድል እጅግ የጠበበ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብን በአግባቡ አደራጅቶና አታግሎ ለውጥ ለማምጣት የሚያበቃ ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል ስለሌለ እሳቸውንና የእሳቸውን “ክሊክ” ከስልጣን ማውረድ በቀላሉ ላይሳካ ይችላል። ይህንን እውነታ በመገንዘብ በዚህኛው የትግል ጠገግ ከነችግሮቻቸውም ቢሆን በዶ/ር ዐቢይ ስልጣናቸውን የተነጠቁትን ገዥውን ብልጽግና ፓርቲንና መንግስትን ከዶ/ር ዐቢይና በዙሪያቸው ካሉ ጠባብ “ክሊኮች” በተለየ የሀገራችን የወደፊት የፖለቲካ ችግር የመፍትሄ አካል አድርገን ልናያቸው ይገባል።
አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ የቻለ የፖለቲካ ኃይል ካለመኖሩም በተጨማሪ ገዥው ፓርቲ በስሩ ከአስራ ሁለት ሚሊዮን በላይ አባላትን አቅፎ የያዘ ግዙፍ ፓርቲ ስለሆነ፣ የሀገሪቱ መንግስትም ልዩ ልዩ የጸጥታና የቢሮክራሲ መዋቅሮችን በስሩ አካትቶ የያዘ ግዙፍ የሀገሪቱ ተቋም ስለሆነ አሁን ላይ ባለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እነዚህን ተቋማት በመፍትሄ አካልነት ታሣቢ ያላደረገ ትግል በቀላሉ ለውጤት ሊበቃ አይችልም። ስለሆነም ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መርጦ ለስልጣን እንዳበቃቸው ሁሉ አሁንም እርሳቸውን ከስልጣን የማውረዱ ቀዳሚ ኃላፊነት የእራሱ እንደሆነ ተግንዝቦ ሀገረ-መንግስቱ ለይቶለት ከመፍረሱ በፊት ራሱን የትግሉና የመፍትሄው አካል አድርጎ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ትግል ማድረግ ያስፈልጋል::
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የተለያዩ የጸጥታ ተቋማትም ህግን ባልጠበቀ አግባብ የአንድ ግለሰብ ታዛዥና አገልጋይ መሆናቸውን አቁመው በሀገሪቱ ህግ ብቻ በመመራት የሀገረ-መንግስቱን ደህንነት ማስጠበቅ እንዲችሉ የሚያደርግ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል። እርግጥ ነው 31 ዓመት ሙሉ ሀገር የመምራት ዕድል አግኝተው እስከ አሁን የሀገሪቱ ችግር ምንጮች እንጅ የመፍትሄ አካል መሆን ያልቻሉትን ገዥውን ፓርቲና መንግስትን ከዚህ ሁሉ ዓመት ትግል በኋላ የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ መጠበቃችን በራሱ እንደ አንድ አሳዛኝ የራሳችን ድክመትና ውድቀት መታየት የሚገባው ነው። ይሁንና እኛም የ31 ዓመት የትግል ዕድል አግኝተን እያለ እስካሁን አንድ። ጠንካራና አማራጭ የተቃዋሚ ጎራ መፍጠር ሳንችል ቀርተናልና እነርሱን በመፍትሄ አካልነት ለማየት መገደዳችንን ለዚህ ድክመታችን ልንከፍለው የሚገባን ዋጋና ቅጣት አድርገን ልናየው ይገባል።
✓ ጠገግ ሶስት
ከፍ ሲል በጠገግ አንድ እና ሁለት ላይ የተጠቀሱትን አቅጣጫዎች ተጨማሪ የትግል ስልቶች አድርጎ መጠቀም ተገቢ ቢሆንም ብቸኛ አማራጭና ዘላቂ መፍትሄ ሊያስገኙ እንደሚችሉ አማራጮች አድርጎ ማየት ግን ስህተት ይሆናል። ካለፈው ልምዳችን በመነሳት ዶ/ር ዐቢይ በራሳቸው በጎ ፈቃድም ሆነ በፓርቲያቸው ግፊት በቀላሉ ስልጣናቸውን ሊለቁ እንደማይችሉ፣ ገዢው ብልጽግና ፓርቲና መንግስትም ኃላፊነታቸውንና ስልጣናቸውን በአግባቡ ተገንዝበው በቀላሉ የለውጥ ኃይል ሊሆኑ እንደማይችሉ እንረዳለን። ስለሆነም ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ተደርጎ መታየት ያለበት በእነሱ አማካኝነት ሊመጣ በሚችለው ለውጥ መተማመን ሳይሆን ተቃዋሚው ጎራና ህዝቡ ተጠናክረው በራሳቸው ትግል ሊያመጡት በሚችሉት ለውጥ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ አስተማማኝ ለውጥ እንዲመጣ ግን በቅድሚያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያለን ተስፋ መሟጠጥ አለበት እንዳልነው ሁሉ አሁን በስራ ላይ ባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተስፋ መቁረጥ አለብን። “ተስፋ መቁረጥ አለብን” ሲባል ግን ‘አንድን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ በአግባቡ መገንዘብ መቻል’ እና ‘ተስፋ ቆርጦ ትግልን ማቆም’ የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸውን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል። ህዝቡ በተቃዋሚው ጎራ ተስፋ እንዲቆርጥ የምንፈልገውም “እነሱ ነፃ ያወጡኛል” ከሚል አጉል ተስፋ ወጥቶ በተሻለ ቁጭትና ዕልህ ትግሉን ለማጠናከር የተግባር ርብርብ እንዲያደርግ ለማስቻል ነው።
ህዝቡ በአንድ በኩል አሁን በስራ ላይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከድክመት ወጥተው እንዲጠናከሩ በዙሪያቸው እየተደራጀ በሃሳብ፣ በገንዘብ፣ በጊዜና በጉልበት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግና በጋራ ተባብረው እንዲሰሩም አስፈላጊውን ግፊትና ጫና ማድረግ አለበት። ይህንን ማድረግና በስራ ላይ የሚገኙትን ተቃዋሚዎች ማጠናከር ካልተቻለም አዳዲስ ፓርቲዎችን በማቋቋም ጭምር ሰላማዊ ትግሉ እንዲጠናከርና ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችል ጥረት ሊያደርግ ይገባል። በተለይም የሀገሪቱ ልሂቃን ከገለልተኝነት፣ ከታዛቢነትና ከሩቅ ተቺነት ሚናቸው ወጥተው እውነተኛ የለውጥ ኃይል ወደ መሆን መሸጋገር አለባቸው።
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከእስካሁኑ ድክመታችን በአግባቡ ተምረን፣ በመካከላችን ያለውን ያለፈ ቁርሾና ቂም-በቀል ይቅር ተባብለን፣ የጎንዮሽ ቅራኔዎችንና መጠላለፍን እርግፍ አድርገን ትተንና ሲቻልም ያለፉ ጥፋቶቻችንን በይፋ ተናዘን፣ የሀገረ-መንግስቱን ህልውና ለመታደግ በሚያስችል መለስተኛ ፕሮግራም ተሰባስበንና ተጠናክረን መውጣት አለብን። ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዙሪያ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ ምን ያህል በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በድንገት ሊፈራርስ እንደሚችልና በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ በህልውና አደጋ ላይ ልትወድቅ እንደምትችል በገሃድ አይተናል። እንዲህ አይነቱን አደጋ መታደግ የሚቻለው በጠንካራ የተቀዋሚ ጎራ መኖር ብቻ ስለሆነ ተቃዋሚውን ጎራ የማጠናከሩ ጥረት ነገ ሳይሆን ዛሬ መጀመር አለበት።
በአጠቃላይ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ በብቸኝነት የተቆጣጠሩት ዶ/ር ዐቢይ፣ ሀገሪቱን በአግባቡ መምራት ያለበትን መሪ የመምረጥና የመሻር ስልጣን ያለው ገዥው ፓርቲና መንግስት፣ የስልጣን ክፍተት ተፈጥሮ ሀገሪቱ የህልውና አደጋ ውስጥ እንዳትገባ የመታደግ ኃላፊነት ያለባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡና በጊዜው መወጣት አለባቸው። ሲቻል ሶስቱም፣ ካልተቻለም ከሶስቱ ሁለቱ፣ ይህም ካልተቻለ ቢያንስ ከሶስቱ አንዱ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ካልቻሉ በሀገሪቱ ዘላቂ ለውጥ ሊመጣ አይችልም።
ለውጥ አይመጣም ሲባልም እንደ እስካሁኑ አምባገነን በሆነ መንግስት እየተገዛን፣ በመልካም አስተዳደር እጦት እየተሰቃየን፣ እርስ በእርስ እየተዋጋንና በድህነት እየማቀቅን እንደ ሀገር የመቀጠል ዕድል ይኖራል ማለት አይደለም። የወደፊቱ ዕድላችን ከዚህ የተለየና የባሰ የማይሆን ቢሆንማ ኖሮ እንዲያውም እራሳችንን እንደ ዕድለኛ በቆጠርን ነበር። ከእንግዲህ የሚጠብቀን አደጋ ለይቶልን መንግስት-አልባ እና ሀገር-የለሽ መሆን ነው። የአሁኑን ወቅት ካለፈው በተለየ ‘የመጨረሻው መጀመሪያ’ ሳይሆን ‘የመጨረሻው መጨረሻ’ የሚያደርገውም በዚህ ዓይነት አደገኛ የውድቀት መስቀለኛ መንገድ ላይ የምንገኝ በመሆኑ ነው።
ይህ ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ለትግሉ ውጤታማነት የታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አስተዋጽኦም እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። የወቅቱን የዶ/ር ዐቢይ የአገዛዝ ዘመን ከሁሉም የተለየ የሚያደርገው ታዋቂና አዋቂ የሆኑ ልሂቃኖቻችን ሁሉ የአደናጋሪ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነው፣ ወይም ጥቅመኛና አድር-ባይ ሆነው፣ ወይም በአጉል ጥላቻ ታውረው፣ ወይም በፍርሃት ቆፈን ተይዘው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዶ/ር ዐቢይ ደጋፊና ተባባሪ መሆናቸው ነው።
ስለ ድፍረቴ አስቀድሜ ይቅርታ እየጠየቅሁ እዚህ ላይከስርዓቱ ጋር በይፋ በመተባበርም ሆነ ዝምታን በመምረጥ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ወይም ሊወጡ ይገባል ብዬ ስለማምንባቸው እንዳንድ ወገኞች የሚከተለውን ጥሪ ላቅርብ።
አንደኛ :- ዶ/ር ለማ መገርሳን፣ አቶ ደመቀ መኮንንን፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የመሳሰላችሁና “በቲም ለማ” ስም በለውጥ ሐዋሪያነት በህዝብ ስትሞገሱ የነበራችሁ ወገኖች - “ህይወታችንን ቁማር አስይዘን አመጣነው” ያላችሁት ለውጥ ከሽፎ ሀገሪቱ እናንተው ለስልጣን ባበቃችሁት መሪ እንዲህ ላለ አደጋ ስትጋለጥ የእናንተ ሚና በዝምታ አድፍጦ መኖር፣ ወይም የአገዛዙ ታዛዥና አገልጋይ መሆን ነበረበትን?”
ሁለተኛ :- አቶ አዲሱ ለገሰን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋን፣ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን፣ አቶ ኩማ ደመቅሳን፣ አቶ ህላዊ ዮሴፍን የመሳሰላችሁና የ17 ዓመቱ መራራ የትጥቅ ጥግል አካል የነበራችሁ ወገኖች - “ሙሉ የወጣትነት ዕድሜአችሁን በታጋይነት ያሳለፋችሁትና ብዙ ሺህ ጓዶቻችሁን በረሃ ላይ ቀብራችሁ የመጣችሁት ታገልንለት ያላችሁት ሀገርና ህዝብ እንዲህ በህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ የፖለቲካ ጡረተኛ ሆናችሁ በዝምታና በትዝብት ለማየት ነበርን?”
ሦስተኛ :- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፣ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋን፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን፣ ዶ/ር በለጠ ሞላን የመሳሰላችሁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሆናችሁና ሹመት ላይ የምትገኙ ወገኖች - “ለብዙ ዓመታት የደከማችሁበት የተቃውሞ ትግል የመጨረሻ ግብ የአምባገነን መሪ ሹመት ተቀብሎ የ አገዛዝ ስርዓት አጃቢና ተባባሪ ለመሆን ነበርን?”
አራተኛ:- ክብርት ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ዘውዴን፣ ዶ/ር ዳንኤል በቀለን፣ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን፣ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የመሳሰላችሁና ከፍተኛ የሞራል ልዕልናና የህዝብ አክብሮት ያተረፋችሁ ወገኖች - “የህይወት ዘመናችሁ የመጨረሻ ስኬት ከአምባገነን ስርዓት ሹመት ተቀብሎ የአገዛዝ መዋቢያ ጌጥ መሆን ነውን?”
አምስተኛ :- ክብርት ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ዘውዴን፣ ዶ/ር ዳንኤል በቀለን፣ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን፣ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የመሳሰላችሁና ከፍተኛ የሞራል ልዕልናና የህዝብ አክብሮት ያተረፋችሁ ወገኖች - “የህይወት ዘመናችሁ የመጨረሻ ስኬት ከአምባገነን ስርዓት ሹመት ተቀብሎ የአገዛዝ መዋቢያ ጌጥ መሆን ነውን?” በ27 ዓመቱ የትግል እንቅስቃሴ የፓርቲ አመራር፣ አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ሆናችሁ በግንባር ቀደምትነት ስትታገሉ የምናውቃችሁ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አርቲስት ታማኝ በየነን፣ አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ የሺዋስ አሰፋን የመሳሰላችሁ ወገኖች - “የዛሬው አገዛዝ በሁለንተናዊ መልኩ ከትናንቱ አገዛዝ የባሰና የከፋ ሆኖ እያለ ዝምታን በመምረጥ ወይም ያልተገባ ሰበብ አስባብ በመስጠት ስርዓቱን ማባባል ወይም በለሆሳስ መደገፍ የመረጣችሁት ቀድሞውንም የትግላችሁ የመጨረሻ ግብ የስርዓት ለውጥ ሳይሆን የህወሐት መውደቅና የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ነበር ማለት ነውን?”
በአጠቃላይ ከዚህ በላይ የተጠቀሳችሁ ወገኖችና በስራችሁ ስኬት የህዝብ አድናቆትንና ክብር ያተረፋችሁ ተዋቂ ስፖርተኞች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ በተለያየ ደረጃ ሀገራችሁን ያገለገላችሁ የቀድሞ ባለስልጣናት፣ ወዘተ …ታዋቂና ባለዝና ብቻ ሳትሆኑ የሀገሩ ልሂቃንም ጭምር ናችሁና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህዝቡ መሪዎች የመሆን ኃላፊነት አለባችሁ።
ዝናና ክብር ያለሀገርና ህዝብ ትርጉም የለውም። በሀገር መፍረስ ከሚመጣው አደጋም ማናችንም ተለይተን አንተርፍም። የወቅቱ ትግል ከፖለቲካ በላይ የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ቢያንስ ስለአገዛዙ ያለንን ተቃውሞ በድፍረትና በጋራ ‘ጮክ ብለን…’ ልናሰማ ይገባል። በአንድ አምባ-ገነን መሪ ምክንያት ሀገር ሲፈርስ ዝም ብሎ ማየት “ባላገር” ነኝ ብሎ ከሚያምን ማንኛውም ዜጋ አይጠበቅምና የታሪክና የትውልድ ሃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ።